በኬንያ አወዛጋቢው ካህን በፍርድ ቤት ነፃ ተባሉ

ጊልበርት ደያ

ልጅ መውለድ ያልቻሉ ጥንዶችን፣ “በጸሎት ልጅ እንድታገኙ አደርጋለኹ፤” በሚሉ፣ በአንድ አወዛጋቢ ካህን ላይ የቀረበውን ክሥ፣ የኬንያ ፍ/ቤት ውድቅ አድርጓል። ክሡ ውድቅ የተደረገው፣ ዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቡ እንደኾነ፣ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

እ.አ.አ በ1990ዎቹ፣ ወደ ብሪታኒያ በማቅናት ኑሯቸውን በዚያ ያደረጉት ጊልበርት ደያ፣ እንደ ቃላቸው በተግባር መፈጸም እንደሚችሉ ለማሳየት፣ በ1999 እና በ2004 ዓመታት መካከል፣ አምስት ሕፃናትን ሰርቀዋል፤ የሚል ክሥ ቀርቦባቸው ነበር።

Your browser doesn’t support HTML5

በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከቶች 10 ኤጲስ ቆጶሳትን መረጡ

ይኹንና ዐቃቤ ሕግ፣ የልጆቹን መጥፋት፣ ከካህኑ ጋራ በቀጥታ የሚያገናኝ በቂ ማስረጃ እንዳላቀረበ ዳኛው ተናግረዋል።

በለንደን፣ በርሚንግሃም፣ ነቲንገሃም፣ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር፣ አብያተ ክርስቲያን ያሏቸው ጊልበርት ደያ፣ በ2017፣ ከእንግሊዝ ወደ ኬንያ ተላልፈው ተሰጥተው፣ በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ እንደነበሩ፣ የኤኤፍፒ ዘገባ አውስቷል።

ደያ እና ባለቤታቸው ሜሪ፣ መውለድ ያልቻሉ ሴቶችን፣ በአራት ወራት ውስጥ በጸሎት እንዲፀንሱ አድርገው፣ “የተኣምር ሕፃናት” ብለው የሚጠሯቸውን ልጆች እንደሚያስገኙ ይናገራሉ።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ “የተኣምር ሕፃናት” የተባሉት፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉ የናይሮቢ መንደሮች፣ የተሰረቁ እንደኾኑ ይናገራል።