ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች ታስረው እንዲመረመሩ ፍ/ቤት ፈቀደ

Your browser doesn’t support HTML5

ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሠራተኞች ታስረው እንዲመረመሩ ፍርድ ቤት ፈቀደ

የፍትሕ መጽሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ ባለፉት ጥቂት ቀናት በቁጥጥር ስር የዋሉ ጋዜጠኞች እና የዩቲዩብ ሚዲያ አዘጋጆች ውስጥ የተወሰኑት ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

ባለፈው ሐሙስ የታሰረው የፍትሕ መጽሔት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ከአስር ቀናት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው “ገበያኑ” የተሰኘ የዩቲዩብ ሚዲያ መስራችና አዘጋጅ ሰለሞን ሹምዬ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ ባለፈው ዓርብ እና ቅዳሜ በቁጥጥር ስር የዋሉት የተለያዩ የዩቲዩብ ሚዲያዎች አዘጋጆች መዓዛ መሐመድ እና በቃሉ አላምረው ለመጀመሪያ ጊዜ መቅረባቸውን ጠበቆቻቸው ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሐሙስ አመሻሽ ላይ ከሥራ ስትወጣ በፖሊስ ተይዛ የነበረችው፣

“የፊንፊኔ ኢንተግሬትድ ብሮድካስቲንግ” ቴሌቪዥን የኦሮምኛ መዝናኛ ዝግጅት አዘጋጅ ሰቦንቱ አህመድ ዛሬ መለቀቋን የጣቢያው ዳይሬክተር ለሚ ታዬ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን በተከታታይ ባወጣው መግለጫ “የሚዲያ ባለሞያዎች እስር የሚዲያ ሕጉን የሚጻረር” መሆኑን በመጥቀስ ባለሙያዎቹ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ የሚዲያ ባለሙያዎች እስር ሕግ የማስከበር እርምጃ አካል መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

በሌላ ዜና ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሞክረዋል በሚል ወንጀል ተጠርጥረው በባሕር ዳር ታስረው የሚገኙት የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴል ጀነራል ተፈራ ማሞ ዛሬ ለሁለተኛ ግዜ ፍ/ቤት ቀርበው፣ ፖሊስ ለምርመራ ተጨማሪ 10 ቀን እንደተፈቀደለት ጠበቃቸው ሸጋው አለበል ገልጸዋል፡፡

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።