በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ረሃብ በአፍሪካ

ፎቶ ፋይል፦ በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው የተሰደዱ እርዳታ ለማግኘት እየተጠባበቁ፤ ባይዶዋ ሶማሊያ 10/12/2022
ፎቶ ፋይል፦ በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው የተሰደዱ እርዳታ ለማግኘት እየተጠባበቁ፤ ባይዶዋ ሶማሊያ 10/12/2022

በአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች የሚከሰቱ ወረርሽኞች እና ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆኑ አጣዳፊ አደጋዎች ቁጥር በዚህ ምዕት ዓመት ከምንጊዜውም በላይ እየጨመሩ መሆናቸው ተዘገበ። ይህም አስቀድሞም 47 ሚሊዮን ሰው ቸነፈር አፋፍ ላይ ባለበት ቀጣና ውስጥ ያለውን የጤና ቀውስ እያባባሰ መሆኑ ተገልጿል።

የሚበዛው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በብርታቱ በአርባ ዓመታት ውስጥ ባልታየ ድርቅ እየተጠቃ ሲሆን አሁንም ለአምስተኛ ጊዜ መደበኛው ዝናብ አይጥልም የሚል ስጋት እንዳንዣበበ መሆኑ ይሰማል።

በሌላ በኩል ደግሞ በጎርፍ እና በግጭቶች የተጎዱ አካባቢዎችም እንዳሉ ይታወቃል።

የለየለት ቸነፈር ይከሰትባቸዋል የሚል ማስጠንቀቂያ ላይ ካሉት የሶማሊያ አካባቢዎች አንዷባይዶዋ መሆኗን የወደብ ከተማዪቱ የድርቅ ምላሽ አስተባባሪ ጄምስ ኢንዲቲያ አመልክተዋል።

በስፋት በቀጠለው ግጭት ምክንያት ብዙ ሰው ከመኖሪያው መፈናቀሉን የጠቆሙት ኢንዲቲያ ድርቅ በተከሰተ ቁጥር ድኅነቱ እየበረታ እንደሚሄድ ተናግረዋል።

ፎቶ ፋይል፦ የሶማሊያ ተፈናቃዮች በዶሎ፣ ሶማሊያ 09/ 19/2022
ፎቶ ፋይል፦ የሶማሊያ ተፈናቃዮች በዶሎ፣ ሶማሊያ 09/ 19/2022

"ዩናይትድ ስቴትስ እና ጀርመንን ከመሳሰሉ ለጋሾች በተገኘው ድጋፍ ሶማሊያ ላይ የተደቀነው የቸነፈር አደጋ ሙሉ በሙሉ ተቀልብሷል ባንልም አዘግይቶታል" ሲሉ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናገሩ። አደጋው ተወግዷል ማለት አለመሆኑን አጥብቀው ሳያስገነዝቡ አላለፉም።

የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚው ዴቪድ ቢዝሊ ይህን ያሉት ስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የዓለም የኢኮኖሚ ጉባዔ ላይ ለአሶሲየትድ ፕሬስ በሰጡት ቃል ነው።

የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ለጋሾች ለዓመታት ባጠቃቸው ድርቅ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ ጉዳት አድርሶባቸዋል ብለው "ለጋሾች ድንቅ በሆነ መንገድ ባይታደጉ ኖሮ ሶማሊያ ውስጥ ከባድ ቸነፈር ገብቷል ብለን ለማወጅ ተዘጋጅተን ነበር" ብለዋል።

በመጪው ሚያዚያ ስራቸውን ለመልቀቅ ያቀዱት የቀድሞው ሪፐብሊካን የደቡብ ካሮላይና አገረ ገዢው ዴቪድ ቢዝሊ የፖለቲካ መስክ ያካበቱትን ተሞክሮ በመጠቀም ከባይደን አስተዳደር እና በፊትም ከትረምፕ አስተዳደር ለዓለም የምግብ ፕሮግራም መጠነ ሰፊ ድጋፍ ለማግኘት እንደቻሉ ይነገርላቸዋል።

ባለፈው ወር የተመድ እና ሌሎች አካላት ባወጡት ሪፖርት 8 ሚሊዮን ሶማሊያውያን በአስከፊ የምግብ ዋስትና ችግር ላይ እንዳሉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ 411 ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች።

ቢዝሊ እአአ በ2017 ዋና ሥራ አስኪያጅነቱን ሲይዙ በዓለም ዙሪያ የምግብ ዋስትና ዕጦት ላይ የነበሩት ሰዎች ቁጥር 80 ሚሊዮን እንደነበር ያወሳው የአሶስየትድ ፕሬስ ዘገባው አሁን በግጭት በአየር ንብረት ለውጥ እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ በተፈጠረው የኢኮኖሚ መቆርቆዝ እና የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ 350 ሚሊዮን መድረሱን አመልክቷል።

ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG