በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ረሃብ በአፍሪካ

ባለፈው የቦረና ድርቅ ዓመታት ከ3 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት ሞተዋል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:19 0:00

በቦረና ዞን ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በቆየው ድርቅ፣ ከ3ነጥብ3 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን፣ የዞኑ የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የዞኑ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሓላፊ ዶክተር ቃሲም ግዩ፣ ለአምስት ተከታታይ የዝናም ወቅቶች በጸናው ድርቅ፣ 46 በመቶ የዞኑ የእንስሳት ሀብት መጥፋቱን፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።

አሁን የድርቁ ወቅት ያለፈ ቢኾንም፣ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ የወደፊት ኑሯቸው እንደሚያሳስባቸው ስጋታቸውን አመልክተዋል፡፡

ወይዘሮ ኤለማ ጀልዴሳ፣ የቦረና ዞን ዱብሉቅ ወረዳ፣ ላፍቶ ቀበሌ ማኅበር ነዋሪ ናት። የአምስት ልጆች እናት እንደኾነች የምትናገረው ወይዘሮ ኤለማ፣ ድርቁ ባዶ እጃቸውን ካስቀራቸው መካከል አንዷ ናት።

“ባለቤቴ እኔን ጨምሮ ሦስት ሚስቶች አሉት፡፡ ድርቁ ሳያራቁተን በፊት፣ ከበረት የምናሠማራቸው 50 የሚደርሱ ከብቶች ነበሩን፡፡ አሁን አንዲት ጥጃ እንኳን አልቀረችልንም፡፡ የእኛ ቤተሰብ፣ ከአማቻችንን ቤት ጋራ አራት ቤቶች አሉት፡፡ ከእኔ ብቻ አምስት ልጆች ተወልደዋል፡፡ የጣውንቶቼ ጨምሮ በአጠቃላይ ወደ ዐሥር ይኾናሉ። ከቤተሰባችን ሰው ቢታመም ወይም የኾነ እክል ቢገጥመው፣ የምንሰጠው ነገር የለንም፡፡ ይህ ፈጣሪ ያመጣው ነገር ነው።”

አቶ ገርብች ዳለቻም፣ በላፍቶ ቀበሌ ነዋሪ ሲኾኑ ፤ “ቀደም ሲል በባንክ የነበረኝን ተቀማጭ፣ ለከብቶቹ መኖ በመግዛት ነው የጨረስኹት፡፡ ኾኖም አሁን፣ ከ180 ከብቶች የቀሩኝ ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ ከነበሩኝ ከ200 በላይ ፍየሎች፣ አሁን የተረፉት አምስት ብቻ ናቸው፡፡” ይላሉ።

አክለውም፤ “በጎቹ ደግሞ 150 ነበሩ፤ አሁን ያሉት ሰባቱ ብቻ ናቸው። ድርቁ ይህን ያህል ሀብት አውድሞብኛል፡፡ አብዛኞቹ ነዋሪዎችም፣ እንደ እኔ ያለ ጉዳት ነው የደረሰባቸው፡፡ ከእነርሱም፣ የቤት እንስሶቻቸው ያለቁባቸው ሰዎች አኀዝ ይበልጣል ባይ ነኝ። ምክንያቱም፣ በዚኽ በላፍቶ ቀበሌ ካሉት ከ600 በላይ አባወራዎች፣ አንድ ወይ ሁለት ከብት በእጃቸው የተረፈላቸው፣ ከ20 ወይ ከ30 ሰው አይበልጡም።” ብለዋል።

ቦረና ዞን፣ በተለይ በቀንድ ከብቶች የሚታወቅ የአርብቶ አደሩ አካባቢ ነው። በፊት በየአውራ መንገዱ የሚታዩት እንስሳት፣ በድርቁ በብዛት ስለ ሞቱ፣ በገጠሩ አካባቢ ሳይቀር የሚታየው የከብቶች ቁጥር በጣም አናሳ ነው።

ዶክተር ቃሲም ጉዮ፣ የቦረና ዞን የግብርና እና የእንስሳት ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሓላፊ ናቸው።

“በቦረና ዞን ለአምስት የዝናም ወቅቶች ዝናም በመጥፋቱ፣ የሞቱት የቤት እንስሳት ቁጥር፣ ከ3ነጥብ3 ሚሊዮን በላይ ነው። ከ46 በመቶ በላይ የሚኾነው የዞኑ የእንስሳት ሀብት በድርቁ ጠፍቷል፡፡” ካሉ በኋላ “በቦረና፣ እንስሳት ግልጋሎት የሚሰጡት፥ ለምግብ እና ለምግብ ተዋጽኦ ብቻ አይደለም፡፡ የተለያዩ ባህላዊ በዓላት የሚከናወኑት በዚኹ ሀብት ነው፤ የክብርም ማሳያ ናቸው። ከዚኽ አኳያ፣ የድርቁ ጉዳት በነዋሪው ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ቀላል አይኾንም።” ይላሉ።

አቶ ማልቸ ዳለቻ፣ የዱብሉቅ ወረዳ የእንስሳት ሀብት ጽሕፈት ቤት ባልደረባ፣ በተለይ በዚኽ አስከፊ ድርቅ፣ ክፉኛ ያለቁት ከብቶች እንደኾኑ ይናገራሉ።

“ድርቁን ተቋቁመው የተረፉት ከብቶች ከ20 በመቶ አይበልጡም፡፡ የዱብሉቅ ወረዳ፣ በከብት ሀብት፣ በቦረና ቀደም ከኾኑት አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት፣ ከ150 ሺሕ በላይ ከብቶች ነበሩ፡፡ አሁን የተረፉት 34ሺሕ ቢኾኑ ነው። የእያንዳንዱ ነዋሪ ኢኮኖሚ እና የኅብረተሰቡ ባህላዊ ዕሤት፣ በእንስሳት ሀብት ላይ የተመረኮዘ ስለኾነ፣ ነዋሪው በጣም ተጎድቷል፡፡”

በቦረና ዞን በ“ቡሳ ጎኖፋ” የመረዳዳት ባህል መሠረት፣ እንስሶቻቸው ከእጃቸው ላለቁባቸው ነዋሪዎች በሙሉ እየተከፋፈሉ በመዳረስ ላይ ናቸው፡፡ ኾኖም፣ የተቀረው የእንስሳት ሀብት ውስን ስለኾነ፣ የመንግሥት እና የሌሎች ተቋማትን ድጋፍ እንደሚሹ ይናገራሉ። ለዚኽም፣ የዞኑ ግብርና እና እንስሳት ሀብት ጽሕፈት ቤት በሥራ ላይ መኾኑን፣ ዶክተር ቃሲም ገልጸዋል።

አንድ መቶ ከብት ለሞተበት ሰው፣ መቶዎቹንም እተካልኻለው ማለት አይቻልም፡፡ ይኹን እንጂ፣ የተወሰነ ከብት መተካት አስፈላጊ ስለኾነ፣ ይህን ከክልሉ መንግሥት ጋራ ኾነን እየሠራንበት ነው። ማኅበረሰቡን፣ ወደ ኑሮው እና ቦታው ለመመለስ የሚቻለው፣ በልገሳ ብቻ አይደለም፤ በማስተማርም ነው።

በሌላ በኩል፣ በቦረና፣ “ቦሳ ጎኖፋ” የሚባል የዳበረ የመረዳዳት ባህል አለ፡፡ አንድ ሰው አምስት ፍየሎች ካሉት፣ ለሌለው አንድ ወይ ሁለት በመስጠት፣ ወዳጁን የሚያግዝበት አካሔድ ነው። በዚኽም ራሱ ኅብረተሰቡ፣ ከ200ሺሕ በላይ እንስሳት ከእጃቸው አልቀው ባዶ እጃቸውን ለቀሩት አርሶ አደሮች፣ እርስ በራሱ በመረዳዳት ላይ ነው። መንግሥትም ይህን ዝም ብሎ አይመለከትም፡፡ እኛ ሰዎቹ የሚረዱበትን አካሔድ ለማሳለጥ፣ የርዳታ ምክረ ሐሳቡን ሠርተን ለክልሉ ሓላፊዎች አድርሰናል፤ ምላሽም እየተጠባበቅን ነን። ዶክተር ቃሲም፣ ዞኑ፥ የሣር ምርት መጀመሩን ገልጸው፣ ከብቶችን አርብቶ ከማደር በተጨማሪ፣ ሌሎች የኑሮ ዘይቤዎችን የማበረታቱ ሥራ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የምግብ እጥረት እና ሞት ያጠላባቸው ከ1.9 ሚ. በላይ ሕፃናት መኖራቸውን ዩኒሴፍ አስጠነቀቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:32 0:00

በአፍሪካ ቀንድ፣ እስከ ዛሬ ታይቶ በማይታወቅ መጠነ ሰፊ ረኀብ፣ መፈናቀል፣ የውኃ ዕጦት እና ድህነት ውስጥ የሚገኙ፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት መኖራቸውን፣ ዓለም አቀፉ የሕፃናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ)፣ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከእነርሱም ውስጥ፣ ከ1ነጥብ9 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት፣ ለከፋ የምግብ እጥረት እና ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ፣ ዩኒሴፍ አስጠንቅቋል፡፡

ዩኒሴፍ በመግለጫው፣ ክልሉ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ካስተናገደው አስከፊ ድርቅ እያገገመ ቢኾንም፣ በአካባቢው ለሚገኙ ማኅበረሰቦች የእንስሳት፣ የሰብል እና የኑሮ ውድመት ምክንያት ኾኖ ማለፉን አመልክቷል፡፡

የዩኒሴፍ የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ አካባቢ ዲሬክተር መሐመድ ፎል፣ በምሥራቅ አፍሪካ ያለው ቀውስ፣ “ለሕፃናት ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፤” ብለዋል፡፡

ዲሬክተሩ አክለውም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት እና ቤተሰቦች፣ በሕይወት ለመቆየት ሲሉ፣ ለአደጋ ተጋላጭ በሚያደርጋቸው ኹኔታ፣ ምግብ እና ውኃ ፍለጋ መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም፣ እንደ ምግብ፣ መጠለያ፣ ውኃ እና ትምህርት ያሉ መሠረታዊ አስፈላጊ ነገሮችን እያሳጣቸው እንደኾነ፣ ዲሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

እንደ ዩኒሴፍ መግለጫ፣ አሁን የሚታየው ዝናም መጠነኛ እፎይታን ቢያመጣም፣ ደረቃማው መሬት ውኃውን አቁሮ ማስቀረት ባለመቻሉ፣ የጎርፍ አደጋ አስከትሏል። ይህም ለተጨማሪ መፈናቀል፣ ለበሽታ ተጋላጭነት፣ ለከብቶች እና ለሰብል ብክነት ምክንያት እንደኾነ አስረድቷል፡፡

በሶማልያ የጎርፍ መጥለቅለቅ፥ ቤቶችን፣ የእርሻ መሬቶችንና መሠረተ ልማቶችን ሲያወድም፣ ወደ 219ሺሕ የሚደርሱ ሰዎችን፣ ከቀዬአቸው አፈናቅሏል፤ 22 ሰዎችን ለሞት ዳርጓል። ኢትዮጵያም በጎርፍ ሳቢያ፣ ከፍተኛ ውድመት እና መፈናቀል አስተናግዳለች።

የጎርፍ አደጋው፣ ቀድሞውንም በድርቅ የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጋላጭነት አጠናክሯል፤ ተደራራቢ ተጽእኖም ፈጥሯል።

የኮሌራ በሽታ በብዙ ክልሎች ተዛምቶ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተመዘገቡት ረጅሙ ወረርሽኞች አንዱ ለመኾን መብቃቱ፣ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በመላው ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማልያ፣ 23 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ የምግብ ዋስትና ዕጦት መዳረጋቸውም ተገልጿል።

አስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውና ሕክምና የሚሹ ሕፃናት ቁጥር፣ ካለፈው ዓመት በእጅጉ ከፍ ያለ ሲኾን፣ ይህም ዘላቂ ጉዳት እንዳለው ዩኒሴፍ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡ “ሴቶች እና ሕፃናት፣ ለጾታዊ እና አካላዊ ጥቃት እንዲሁም ለጉልበት ብዝበዛ የመጋለጥ ዕድላቸው እየጨመረ ነው፤” ያለው መግለጫው፣ ቀጣይነት ያለው የኮሌራ፣ የኩፍኝ፣ የወባ እና የሌሎች በሽታዎች ወረርሽኝ፣ በአስከፊ የአየር ኹኔታ እና ደካማ የጤና ሥርዓቶች መባባሱን አስታውሷል፡፡

ዋጋው የናረ የምግብ ዋጋ፣ በአካባቢያዊ ገበያዎች ላይ ጫና ከማሳደሩም በላይ፣ ሕፃናትንና ቤተሰቦቻቸውን ለከፋ ጉዳት ያጋልጣል። የአየር ንብረት ቀውሱ፥ የጅምላ መፈናቀልን፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትንና የበሽታዎችን አስከፊነት ያባብሳል፤ ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2022፣ የለጋሾች ድጋፍ፥ ከ30 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ሕፃናት እና እናቶች፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመከላከል ማገዙን ያመለከተው ዩኒሴፍ፣ በዚኽ ዓመት፣ ተለዋዋጭ የገንዘብ ድጋፍ፣ ለሕፃናት ማገገሚያ ብቻ ሳይኾን፣ ቀጣይ የአየር ንብረት ተጽእኖዎችንና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቋቋም፣ ተከላካይ እና ዘላቂ ሥርዐቶችን ለማዘጋጀት ያለው አስፈላጊነትም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ያለው አስከፊ የአየር ሁኔታ ለውጦችን በሚመለከት አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲል ይህ ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ ግን ህጻናት እና ቤተሰቦች ሙሉ በሙሉ የማገገም እድል ከማግኘታቸው በፊት ቀጣዩ ቀውስ ሊመጣ ይችላል ሲል ማስጠንቀቁን መግለጫውን የጠቀሰው የአሶሴይትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG