በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ረሃብ በአፍሪካ

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የርዳታ ምግብ ሥርጭቱን ማቆሙን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:07 0:00

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም(WFP)፣ ለኢትዮጵያ ተጎጂዎች ሲያሠራጭ የቆየውን የምግብ ርዳታ፣ “ስርቆት በመንሰራፋቱ” ምክንያት ለጊዜው ማቆሙን፣ ዛሬ አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የርዳታ ምግብ የማቆም ውሳኔውን ይፋ ያደረገው፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ተመሳሳይ ርምጃ መውሰዷን፣ በዩኤስኤአይዲ በኩል ካሳወቀች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ውሳኔን ተከትሎ፣ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ በኾነችው ሀገር፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የበለጠ ሊጨምር ይችላል፤ የሚል ስጋት አይሏል።

ውሳኔውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዲሬክተር ሲንዲ ማኬይን፣ “የምግብ ርዳታ ለተረጂዎች እንዳይደርስ ማድረግ በፍጹም ተቀባይነት የለውም፤” ያሉ ሲኾን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሓላፊነት ያለባቸውን ለማጣራትና ተጠያቂ ለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቁም ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ፣ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ባልታየው ድርቅ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀውና በ10ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋው ግጭት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ሰዎች፣ የምግብ ርዳታ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በነዚኽ ሁለት ቀውሶች ምክንያት የተጎዱ፣ ሰባት ሚሊየን ሰዎችን ሲረዳ ቆይቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም(WFP) እና የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት(USAID)፣ ለውሳኔያቸው ምክንያት በኾነው፣ “የርዳታ ለተጎጂው አለመድረስ” ጉዳይ፣ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ የዜና አውታሮች የተመለከቱትና ለለጋሽ አካላት የተሠራጨው መግለጫ፣ በፌደራል እና በክልል መንግሥታት ባለሥልጣናት የተቀናጀ የጥቅም ትስስር፣ የርዳታ ምግብ፣ ወደ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ክፍሎች እንደሚዘዋወር አመልክቷል።

በዋናነት የሚያሳስበን፣ በእኛ ድጋፍ ላይ ጥገኛ የኾኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ረኀብተኞች ጉዳይ ነው፤ ያሉት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዲሬክተር፣ በተቻለ ፍጥነት ሥራችንን ለመቀጠል፣ ከሁሉም አጋሮቻችን ጋራ ያለመታከት እንሠራለን፤ ብለዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፥ ለሕፃናት፣ ለነፍሰ ጡሮች እና ለሚያጠቡ እናቶች የሚደረግ የተመጣጠነ ምግብ ርዳታ፣ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብሮች፣ የአርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ዐቅም ለመገንባት የሚደረጉ ድጋፎች ግን ሳይቋረጡ እንደሚቀጥሉ በመግለጫው አስታውቋል።

በሮይተርስ የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ።

የርዳታ እህል ለተረጂ ያልደረሰው “በመጠነ ሰፊና የተቀናጀ ዘመቻ” እንደኾነ ዩኤስኤአይዲ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:08 0:00

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምትለግሰው የምግብ ርዳታ እንዲቋረጥ ያደረገችው፣ “ለተረጂው አይደርስም” በማለት እንደኾነ በይፋ አስታወቀች፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (USAID)፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የምግብ ርዳታ፣ “ለተረጂዎች አይደርስም” ሲል፣ ርዳታውን ማቋረጡን፣ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።

“ለተቸገረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መድረስ የሚገባው የምግብ ርዳታ፣ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲቀየስ የሚያደርግ፣ መጠነ ሰፊ እና የተቀናጀ ዘመቻ መኖሩን”፣ ዩኤስኤአይዲ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በመተባበር ባደረጉት ማጣራት ከድምዳሜ ላይ መድረሳቸውን፣ የድርጅቱ ቃል አቀባይ በይፋ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።

ኾኖም፣ ርዳታው ለተረጂ ወገኖች እንዳይደርስ ከሚደረገው ዘመቻ ጀርባ ያለው ማን እንደኾነ፣ በመግለጫው ተለይቶ አልጠቀሰም። ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአፍሪካ ቀንድንና አካባቢውን ክፉኛ ከጎዳው ድርቅ እና በቅርቡ ከአበቃው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋራ በተያያዘ፣ ለርዳታ ጠባቂነት የተጋለጡትን ጨምሮ፣ ቁጥሩ 20 ሚልዮን ለሚደርሰው ተረጂ ሕዝብ ዋናዋ ለጋሽ ሃገር ናት።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በተመለከተው እና በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ የረድኤት ሥራ ለሚያከናውኑ የውጭ ለጋሽ ቡድኖች የቀረበ አንድ ሰነድ፣ “የርዳታ ምግቡ፥ ለአገሪቱ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎች እንዲሰጥ ተደርጓል፤” ብሎ፣ ዩኤስኤአይዲ እንደሚያምን ይጠቁማል።

ርዳታውን ከታለመለት ዓላማ ውጭ የማዋሉ ድርጊት፣ “በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት አካላት የተቀነባበረ ዘመቻ፣ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ወታደራዊ ክፍሎች፣ ለሰብአዊ ርዳታ የመጣው ምግብ ተጠቃሚ ናቸው፤” ሲል፣ ዩኤስኤአይዲ’ን ያካተተው ይኸው የለጋሾች ቡድን ሰነድ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የመከላከያ ሠራዊቱ ቃል አቀባዮች፣ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ለጊዜው አፋጣኝ ምላሽ አልሰጡም። ዩኤስኤአይዲ’ም በበኩሉ፣ ሪፖርቱን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በሳዑዲ አረቢያ እየተካሔደ ካለው ጉባኤ በትይዩ፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ከኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን ጋራ በጉዳዩ ዙሪያ ተወያይተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የሁለቱን ባለሥልጣናት ውይይት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በጉዳዩ ላይ ሙሉ ምርመራ ለማካሔድ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ተባብሮ ለመሥራት የገባውን ቃል፣ ብሊንከን በአዎንታ መቀበላቸውን አመልክቷል።

በተያያዘም፣ የርዳታ ምግብ እደላ ሥርዐቱ አመኔታ ሊጣልበት እንደሚችል እንደታመነ፣ የሥርጭት ሥራውን ለማስቀጠል ድርጅታቸው የሚያቅድ መኾኑን፣ የዩኤስኤአይዲ’ው ቃል አቀባይ ጨምረው አመልክተዋል።

ዩኤስኤአይዲ እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም(WFP)፣ በትግራይ ክልል፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ ርዳታ፣ ከታለመለት ዓላማ ውጭ እንዲውል መደረጉን የሚያሳይ መረጃ ከእጃቸው መግባቱን ተከትሎ፣ ካለፈው ወር አንሥቶ በክልሉ ያደርጉት የነበረውን የምግብ እደላ ማቋረጣቸው ይታወሳል።

በትግራይ ክልል፣ በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው እና አያሌ ሺሕዎች ያለቁበት፣ እንዲሁም በ100ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለቸነፈር መሰል የረኀብ አደጋ እንዲጋለጡ ምክንያት የኾነው ጦርነት፣ ባለፈው ጥቅምት ወር፣ በደቡብ አፍሪካ - ፕሪቶርያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ማብቃቱ ይታወቃል።

ዩኤስኤአይዲ፣ እ.አ.አ በ2022 የበጀት ዓመት፣ 1ነጥብ5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ ያለው ሰብአዊ ርዳታ ለኢትዮጵያ ሰጥቷል። ከዚኽም ውስጥ የሚበዛው፣ በምግብ ርዳታ መልክ የተሰጠ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ትላንት ረቡዕ፣ በለጋሽ ድርጅቶች መካከል የተሠራጨው የቡድኑ ሰነድ፣ ለጋሾች የሚሰጡትን ርዳታ፣ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን በመሳሰሉ “አማራጭ ዘዴዎች” ለተረጂው ወገን ማድረስ ይችሉ ዘንድ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲፈቅድ ይመክራል።

ሰነዱ አክሎም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፥ ድርጊቱን በማውገዝ እና የርዳታ ሠራተኞች እንግልት እንዳይደርስባቸው በመጠየቅ፣ ግልጽ መግለጫ እንዲያወጣ፣ ለጋሾች ጥሪ እንዲያቀርቡ ያሳስባል።

በተመሳሳይ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ፣ በመላው ኢትዮጵያ “በተቀነባበረ መንገድ” ይፈጸማል ያለውን የርዳታ ምግብ ከታለመበት ዓላማ ውጭ የማዋል ድርጊት እየመረመረ እንደኾነ፣ ባለፈው ሳምንት የድርጅቱ ምክትል ዲሬክተር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያገለግሉ ሠራተኞቻቸው የጻፉት የኢሜል መልዕክት ጠቁሟል። ይኹንና፣ ይህን ተንተርሶ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ተቋሙ፣ እስከ አሁን የሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያ የለም፡፡

ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG